ቅዱሳን በነገስታት ልብ እና ክብር ተነስተው ማየት
ለወደደንና ከኅጢአታችንም በደሙ ነጻ ላውጣን፣ አምላኩንና አባቱን እንድናገለግልም መንግሥትና ካህናት ላደረገን፣ ለእርሱ ክብርና ኅይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን አሜን።
ራዕይ1፡6
የነገስታት አገልግሎት ዳይሬክተር
ቅዱሳን በነገስታት ልብ እና ክብር ተነስተው ማየት
ለመንግስቱ ነፍሳትን መማረክ፣ መገንባት እና መላክ
የሰማያዊ መንግስትን ሕይወት እና ክብር መግለጥ
በብሉይ ኪዳን ዘመን፤ ነገስታት የእስራኤልን ሕዝብ በሙሴ ሕግ እና ስርዓት መሰረት፤ በእግዚአብሔር ተቀብተው እና የእርሱ ተወካይ ሆነው፤ ይገዙ እና ያስተዳድሩ ነበር። ነገስታት ሁለት ታላላቅ ኃላፊነቶችን ይሸከሙ የነበረ ሲሆን በመጀመሪያ በእረኝነት ልብ: የጠፋውን የመፈለግ፣ የባዘነውን የመመለስ፣ የተሰበረውን የመጠገን፣ የደከመውን የማጽናት፣ በፍርድ ፍትህን የማስፈን እና የእግዚአብሄርን ሕዝብ እና ግዛት ከጠላት የመጠበቅ ኃላፊነቶች ይሸከሙ ነበር።
ሁለተኛ ደግሞ በጦረኛ ልብ: አሕዛብን ለእግዚአብሄር ርስት እንዲሆኑ የመማረክ እና የአሕዛብን ግዛት የእግዚአብሔር መንግስት (የእስራኤል መንግስት) ግዛት እንዲሆን የመውረስ ኃላፊነቶች ይሸከሙ ነበር። ነገስታቱ እነዚህን ታላላቅ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችላቸው የማህበረሰብ መዋቅር እና የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ነበራቸው።
ማህበረሰቡ በነገድ፣ በጎሳ እና በቤተሰብ የተዋቀረ ሲሆን የመንግስት አስተዳደር ስርዓቱም፤ ይህንኑ የማህበረሰብ መዋቅር ተከትሎ የተዘረጋ ነበር። ይህ የማህበረሰብ መዋቅር የነገስታቱን የኃላፊነት ሸክም ከቤተመንግስት እስከ ቤተሰብ ድረስ የማውረድ እና የማካፈል እድልን የሚሰጥ ስለነበር፤ የእያንዳንዱ ቤተሰብ መሪ፤ የንጉሱን የሕይወት ምሳሌ በመከተል፤ ለራሱ ቤተሰብ እንደ ንጉስ የመቆም እና የመመላለስ ኃላፊነት ነበረበት። ነገስታቱ ለመንግስታቸው ኃይል የሚሆን ሰራዊት ይገነቡ የነበረውም፤ ከየቤተሰቡ በሚሰበስቧቸው እድሜያቸው ሃያ እና ከዚያ በላይ በሆኑ፥ ጋሻ እና ጦር መያዝ በሚችሉ፥ ጎበዞች ነበር። ይህ የነገስታት ሕይወት በቤተመንግስት ውስጥ ብቻ የሚገለጥ ሳይሆን በእያንዳንዱ የእስራኤል ሕዝብ ቤተሰብ ውስጥ የሚታይ ነበር።
ብሉይ ኪዳን የአዲስ ኪዳን ጥላ ሲሆን፤ አዲስ ኪዳን ደግሞ በአንጻሩ የብሉይ ኪዳን መንፈሳዊ አካል ነው። በአዲስ ኪዳን፥ ነገስታት መንፈሳዊ ስልጣን እና ክብር እንጂ አካላዊ ዙፋን መገለጫቸው አይደለም። ይህ እውነታ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት የተገለጠ እውነት ነበር። ይከተሉት የነበሩትም ደቀመዛሙርት፤ በመንፈስ ተረድተው፤ እርሱ የእግዚአብሄር ልጅ ክርስቶስ መሆኑን አምነው እና መስክረው ነበር (ሐዋ 2፥ 36) ። ኢየሱስ ሲወለድ የአይሁድ ንጉስ እንደተወለደ መጽሐፍ ቅዱሳችን ቢመሰክርም፤ ዳሩ ግን በሄሮድስም ሆነ በጲላጦስ ዙፋን ተቀምጦ የእስራኤልን ሕዝብ እና መንግስት ሲመራ አንመለከተውም፤ ይህም መንግስቱ እና ዙፋኑ ሰማያዊ እና መንፈሳዊ እንደሆነ እንድንረዳ ያደርገናል።
በተመሳሳይ መልኩ በራዕይ 1፡6 (አ.መ.ት) ላይ ‘’አምላኩንና አባቱን እንድናገለግልም መንግሥትና (ነገስታትና) ካህናት ላደረገን፣ . . .” በማለት አማኞች ሁሉ፥ መንፈሳዊ የነገስታት ስልጣን እና ክብር በክርስቶስ እንደተሰጠን ይገልጥልናል። የአዲስ ኪዳን ነገስታት፤ በክርስቶስ የእረኝነት ልብ፥ የጠፋውን የመፈለግ፣ የባዘነውን የመመለስ፣ የተሰበረውን የመጠገን፣ የደከመውን የማጽናት፣ በፍርድ ፍትህን የማስፈን እና የእግዚአብሔርን ሕዝብ እና ግዛት ከጠላት የመጠበቅ፥ እንዲሁም በመንፈሳዊ ጦረኛ ልብ ደግሞ፥ ነፍሳትን ለእግዚአብሔር መንግስት የመማረክ እና የእግዚአብሔርን መንግስት ግዛት በኅይል የማስፋት ተልዕኮ እና ኃላፊነት በክርስቶስ ተሸክመዋል። ይህ የነገስታት ሸክም በአብ ቀኝ ከተቀመጠው እና የሁላችን ንጉስ እና ጌታ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ፤ አካሉ ወደሆነችው ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚፈስ መንፈሳዊ ሸክም እና ተልዕኮ ነው።
ቅዱሳን እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ፥ መንፈሳዊ ሕብረት የሚያደርጉበት ሰማያዊ ቤተሰብ ነው። ቅዱሳን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚገነቡበት እና የእግዚአብሔርን መንግስት ለማገልገል የሚሰማሩበት ሕያው የሆነ ሕብረት ነው። አንድ የንጉሱ ቤተሰብ ከ10 - 15 የቤተሰብ አባላትን ሊይዝ የሚችል ሲሆን እያንዳንዱ ቤተሰብ በንጉሱ ቤተሰብ መሪ ይመራል።
ቤተሰብ የከተማ መዋቅራዊ እና ተግባራዊ ክፍል ነው። (Family is the structural and functional unit of a city) በተመሳሳይ መልኩ ከተማ የመንግስት መዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ክፍል ነው። የንጉሱ ቤተሰብ ትንሹ ቤተክርስቲያን ሲሆን እግዚአብሄር በረከቱን እና ሕይወቱን በዚህ ስፍራ አዟል።
ኢየሱስ በማቴ 12፥ 49-50 ላይ "በእጁም ወደ ደቀመዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ "እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።" በማለት የሰማያዊውን ቤተሰብ መሰረት አስተዋውቆናል።
የንጉሱ ቤተሰብ አራት የተለያዩ ሳምንታዊ ስብሰባዎችን የሚያደርግ ሲሆን እያንዳንዱ መርሃግብር የቤተሰቡን ተልዕኮ ለማስፈጸም ታልሞ የተዋቀረ ነው።
1. የነገስታት አዋጅ ስብሰባ (Kings Decree Meeting) 2. የነገስታት ማዕድ ስብሰባ (Royal Feast Meeting ) 3. የመንግስቱ ተልዕኮ ስብሰባ (Kingdom Mission Meeting) 4. የምስጋና ስብሰባ (Thanksgiving Meeting)